እጆች ሁሉ እንደ ወይዘሮ ዘመናይ ለተቸገሩ ወገኖች ይዘርጉ!

March 4, 2022

ባሕር ዳር: የካቲት 19/2014 ዓ.ም (አሚኮ) ለረጂም ጊዜ የቆየ የኩላሊት ሕመም ያሰቃያቸዋል፣ የካንሠር ታማሚ መሆናቸውንም ነግረውናል። በሌላ በኩል ደግሞ ኤች አይ ቪ ቫይረስ በደማቸው ስላለ መድኃኒት ይወስዳሉ። ወይዘሮ ዘመናይ በላይነህ በየእለቱ የሰቆቃ ሕይወት እየመሩ ያሉ የሁለት የልጆች እናት ናቸው። እሳቸው ሕክምና ተቋም ሄዶ የጤናቸውን ጉዳይ ለመከታተል ይቅርና ልጆቻቸውን በቅጡ ቁርስ መግበው ምሳ መድገም የሚያስችል አቅም የላቸውም። ኑሯቸውን የሚገፉት በደሳሳ ኮንቴይነር ውስጥ እንደሆነ እና ለነፍሱ ያለ በሚያደርግላቸው እገዛ ቀን እየገፉ መሆኑን ነው የሚናገሩት። ያም ሆኖ ከጊዜ ወደ ጊዜ የጤናቸው ሁኔታ አሳሳቢ እየሆነባቸው ነው። አሁን እንደልባቸው መንቀሳቀስ በማይችሉበት ደረጃ ላይ መሆናቸውን በተለይ ለአሚኮ ተናግረዋል። ለፈተና የተፈጠሩ እስኪመስል በአንድ በኩል ድህነት፣ በሌላ በኩል የኑሮ ውድነቱና የጤናቸው ጉዳይ የተወሳሰበ ችግር ሆኖባቸዋል። በተለይ ሕመማቸው እየተባባሰ በሄደ ቁጥር የልጆቻቸውን እጣ ፋንታ እያሰቡ ይጨነቃሉ፣ አብዝተውም ያለቅሳሉ።

ዛሬ ግን በመጠኑም ቢሆን የተስፋ ጭላንጭል እንዲመለከቱ ምክንያት አግኝተዋል። የአቶ ምስጋናው ቤተሰቦች እንደ ወይዘሮ ዘመናይ ላሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች የአንድ ዓመት የጤና መድኅን ክፍያ ፈጽመውላቸዋል።

በባሕር ዳር ከተማ ለሚገኙ 1 ሺህ 500 አቅመ ደካሞች፣ አካል ጉዳተኞች፣ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላላቸው አባ ወራ እና እማዎራዎች ነው የአቶ ምስጋናው ቤተሰቦች የአንድ ዓመት የጤና መድኅን ክፍያ የሸፈኑት። 7 ሺህ ገደማ ሰዎች የጤና አገልግሎቱ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል። እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሀብት አመንጭተው ራሳቸውን እስከሚችሉ ድረስ በቋሚነት የጤና መድኅን ተጠቃሚ ሆነው እንደሚዘልቁም ተገልጿል። ይህ መልካም ተግባር ወይዘሮ ዘመናይ በላይነህ የመኖር ተስፋ እንዲሰንቁ አድርጓቸዋል። ምንም እንኳን ችግራቸው ከተደረገላቸው ድጋፍ በላይ ቢሆንም የሕክምና ወጪያቸው መሸፈኑ ጭንቀታቸውን በትንሹም ቢሆን ቀንሶላቸዋል። ለተደረገላቸው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል። እንደ ወይዘሮ ዘመናይ ሁሉ ድጋፉ በሕክምና የሚያጋጥማቸውን ችግር እንደሚፈታ ሌሎች የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል፤ ምስጋናም አቅርበዋል።

ድጋፉ በዚህ ብቻ አላበቃም። የአቶ ምስጋናው ቤተሰቦች የተቸገሩ ወገኖችን በተደራጀና ቀጣይነት ባለው መልኩ ለመደገፍ እንዲሁም የበጎ አድራጎት ሥራውን ይበልጥ ለማሳደግ ዛሬ "የባሕር ዳር በጎ አድራጎት ድርጅትን" መሥርተው ይፋ አድርገዋል። የድርጅቱ መሥራች አባል እና የቤአኤካ ጀነራል ቢዝነስ ሥራ አስፈጻሚ ካሳሁን ምስጋናው እንዳሉት የአቶ ምስጋናው ቤተሰቦች ከዚህ በፊትም በተናጠል በርካታ የበጎ አድራጎት ተግባራትን አከናውነዋል። እንቅስቃሴውን ይበልጥ ውጤታማ እና ዘላቂ ለማድረግም ድርጅቱን መመስረት አስፈልጓል። በዚህ መነሻነት ቤተሰቡ ተሰባስቦ የመሰረቱትን ድርጅት ዛሬ ይፋ አድርገዋል። ድርጅቱ በቀጣይ በርካታ ተግባራትን ለማከናወን አስቧል። በጤና ዘርፍ የተስተዋለው ችግር እጅግ ውስብስብ በመሆኑ ቀዳሚ ትኩረት እንደተሰጠውም ተመላክቷል። መንግሥት የጀመረው የጤና መድኅን አገልግሎት አመቺ በመሆኑ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የከፋ ችግር ያለባቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች በመለየት የጤና መድኅን ክፍያ ተፈጽሟል። በቀጣይም በከተማ ግብርና፣ በትምሕርት፣ በስፖርት፣ እና የሥራ እድል ፈጠራን ጨምሮ አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች፣ ሴቶችና ሕጻናትን ታሳቢ ባደረጉ ሰባት ዘርፎች የበጎ አድራጎት ተግባር ለመሥራት ዕቅድ ተይዟል ብለዋል አቶ ካሳሁን።

ሁሉንም ነገር የመንግሥት አድርገን ማየት አግባብ አይደለም ያሉት ባለሀብቱ የተሻለ አቅም ያለው ሁሉ በሚችለው አቅም የተቸገሩትን እንዲረዳ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የባሕር ዳር በጎ አድራጎት ድርጅትን መመስረት የሚመለከቱ ጓደኞቼ የዚህ ተግባር ተሳታፊ ከመሆን ወደ ኋላ እንደማይሉ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል። ለጊዜው በቤተሰብ ደረጃ ድርጅቱ ቢመሠረትም ፍላጎት ላለው ሁሉ በሩ ክፍት መሆኑንም ነው የገለጹት። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል አቡነ አብርሃም ፈጣሪ ለሰው ልጆች ካስተማራቸው መልካም ነገሮች መካከል የተቸገሩትን መርዳት፣ በአቅም እጦት ሰቆቃ ውስጥ የወደቁ፣ የተመኙትን እና የወደዱትን ማድረግ የማይችሉ ወገኖችን መታደግ ዋንኛው እንደሆነ ገልጸዋል። የአቶ ምስጋናው ቤተሰቦች ይህንን መልካም ተግባር በማድረጋቸው የፈጣሪን ፈቃድ ፈጽመዋልና ልንቀና ይገባል ብለዋል አቡነ አብርሃም ባስተላለፉት መልዕክት።

ይህ መልካም ተግባር ቀጣይነት እንዲኖረው ረዳት የሌላቸው ወገኖችን ለመደገፍ፣ በርሃብ የሚሰቃዩትን ለመመገብ፣ የተቸገሩትን ለመርዳትና በጤና መታወክ ለሚቸገሩት አለኝታ የሚሆናቸው ባሕር ዳር በጎ አድራጎት ድርጅት መመስረቱም እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሰናይ ተግባር መሆኑን ነው የገለጹት። "ያለምንም ልዩነት የተቸገረ ሕዝብን ለመርዳት ዝግጁ በመሆናችሁ ኮርተናል" ያሉት አቡነ አብርሃም ውጤቱ ያማረ እንዲሆን ፈጣሪ ይርዳችሁ ብለዋል።

ወይዘሮ ዘበናይ የሕክምና ወጪያቸው ተሸፈነ እንጂ መሠረታዊ ፍላጎታቸው እንዲሟላ አሁንም ተጨማሪ ድጋፍ ይሻሉ። የሚያርፉበት መጠለያ የላቸውም፣ የእለት ጉርስ ችግር አለባቸው። የልጆቻቸው ተስፋ ነገ እንዳይጨልም መማር አለባቸው። እሳቸው የለጋሾችን እጆች ይሻሉ፣ እጃቸውንም ወደ ለጋሾች ዘርግተዋል። ለዚህ ደግሞ እንደነ አቶ ምስጋናው ቤተሰቦች በጎ እናስብ በጎውንም እናድርግ።

ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ